የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ አባል ይሁኑ

ቤተሰብ የሚለው ቃል በፍቺ እና በምሥጢር ሲተነተን ወደላይም ፣ ወደታችም ወደፊትም ወደኋላም ወደግራም ወደቀኝም ያለውን ሥጋዊ የመንፈሳዊ የተዛምዶ ምልአተ ጉባኤ ያሟላና ያካተተ ስም ነው፡፡

ከላይ ወደታች ያለው የቤተሰባዊ ስም ሲብራራ የአቶ እገሌ የወ/ሮ እገሊት ልጆች ወደ ግራ እና ወደቀኝ ያለው ቤተሰባዊ ስያሜ ሲገለጽ እነ እገሌ እነ እገሌ የእነ እገሌ እህት ወንድም አክስት አጎት የእህት ልጅ የወንድም ልጅ ወ.ዘ.ተ በማለት በሁሉም አቅጣጫ ያለውን ሥጋዊ ቤተሰብ የተዛመደ ሐረግ መግለጽ ይቻላል፡፡ ሥጋዊ ቤተሰብ ትሥሥር ይልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብነት የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የድንግል ማርያም ቤተሰቦች ወ.ዘ.ተ በማለት ሰፍቶና ጎልቶ  ይገለጻል፡፡

በዚህ መሠረት የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ ማለት ወደ ላይ የፈጠረው ፣ የመረጠው ሰማያዊ ምስጢርን የገለጠለት እግዚአብሔር ወደጎን እንደነሱ በእነርሱ ምስጋና እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን ያስተማሩት እና የረዱት ቅዱሳን መላእክት ወደታች  የእርሱን ሰማያዊ ምስጋና የዜማ ምሥጢር ቁጥሩን ሳያጎድሉ ብዛቱን ሳይቀንሱ ሥርዓቱን ሳይቀይሩ ሕጉን ሳያፈርሱ ሰማያዊነቱን መንፈሰዊነቱን ሳይሽሩ በሙሉተምረው አውቀው በሙሉ የሚያስተምሩ እና በሙሉ እግዚአብሔርን የሚያሰግኑ እንዲሁም በቅዱስ  ያሬድ ምስጋና ሰማያዊ ድርሰት የእግዚአብሔርን አምላክነት የሚያምኑና የሚመሰክሩ የቅዱስ ያሬድ ዜማው እንዲስፋፋ፣ታሪኩ እንዲታወቅ በእውቀታቸው በጉልበታቸው ፣ በገንዘባቸው እና በጸሎታቸው የሚያገለግሉ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ ይባላሉ፡፡