የስሙ ትርጓሜ 

ያሬድ ማለት ርደት፣ ወሪድ፣ ማለትም መውረድ ማለት ነው፡፡ ከአዳም ስድስተኛ በሆነው በመላልኤል ልጅ በያሬድ ጊዜ ደቂቀ ሴት ከደብር ቅዱስ ወደ ደቂቀ ቃየን ወደ ምድረ ፍዳ ስለወረዱ ያንን ለማስታወስ አባቱ መላልኤል ያሬድ ብሎታል፡፡  “ወጸውዐ ስሞ ያሬድሃ እስመ በመዋዕሊሁ ወረዱ መላእክተ እግዚአብሔር ውስተ ምድር እለ ተሰይሙ ትጉሃነ፣ ስሙን ያሬድ ብሎ ጠራው በእርሱ ዘመን ትጉሃን ተብለው የሚጠሩ የእግዚአብሔር መላእክት (ደቂቀ ሴት) ከደብር ቅዱስ ወደ ምድረ ፍዳ ወርደዋልና ማለት ነው፡፡ መጽ ኩፋሌ 5፤፳1-፳2  በኢትዮጵያም ዳግማዊ ያሬድ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተነሥቶ ሰማያዊውን ልዩ ጣዕመ ዜማ ወደ ኢትዮጵያ የሚያወርድ ነውና ይህንን ለመግለጽ እግዚአብሔር አምላክ በእናቱ እና በአባቱ ላይ አድሮ ያሬድ እንዲባል አድርጓል፡፡ ምስጢሩ ልዩ ጣዕመ ዜማን ከሰማይ የሚያወርድ መሆኑን ያሳያል፡፡ 

ያሬድ ማለት ንብ ማለት ነው፡፡ ንብ የማይቀስመው አበባ እንደሌለ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም ከቅዱሳት መጻሕፍት የማይጠቅሰው የለም፡፡  ከንብ የተገኘ ማር ጣፋጭ ከመኾኑም በላይ ሰሙ መብራት ኾኖ ጨለማን አርቆ ብርሃን በማሳየት ደስ እንደሚያሰኝ የቅዱስ ያሬድም ዜማ ንባቡ ከምስጢሩ ጋር ተዋሕዶ ምእመናንን ደስ ከማሰኘቱም በላይ ለምእመናን ደስታን የሚያበስር፣ ኀይለ ቃሉ  ጨለማ ክሕደትን የሚያርቅ ነው፡፡

ያሬድ ማለት ረአዬ ምስጢር ነጻሬ ኅቡአት “ምስጢር ተመልካች፣ ምስጢር ገላጭ ማለት ነው፡፡” ረአዬ ምስጢር መባሉ የመላእክት ምስጢራት የነበሩትን ጸዋትወ ዜማ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯልና፤ “ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን” (ከቅዱሳን መላእክት በሰማይ የሰማኹት ዜማ ምን ይረቅ! ምን ይጠልቅ !) እንዲል፡፡ ነጻሬ ኅቡአት መባሉ ደግሞ  ኅቡእ (ስውር) የኾነ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የነቢያት፣ የሐዋርያትን ገድል አምልቶ አስፍቶ ስለሚናገር ነው፡፡

Read More…